ህወሃት ጊዜው እየመሸበት ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ቀርቧል — የትግራይ ተወላጆች

ህወሃት ጊዜው እየመሸበት ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረቡን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ። 

የትግራይ ተወላጆች ለኢዜአ እንደገለጹት ቡድኑ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛ በአገርና ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና በደል በርካታ ነው።

በእነዚህ አመታት ለራሱ ህልውና እና አብረውት ለቆሙት ቡድኖች ከመጥቀም ውጭ ለትግራይ ህዝብ “እዚህ ግባ” የሚባል ጥቅም እንዳላስገኘለትም ያምናሉ።

ሆኖም የጥፋት ቡድኑ አሁን ላይ “ጊዜው እየመሸበት” ሲሄድ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመቅረብ መሞከሩን ገልጸዋል።

የትግራይን ልዩ ሃይልና ሚኒሻ ለነፍሱ ማቆያ ለማድረግ የጥፋት መልእክተኛ ማድረጉ ደግሞ የህወሃትን ፍፁም የሆነ ግለኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሙዑዝ ገብረ ህይወትና ወይዘሮ መሰሉ ረዳ የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት ህወሃት የትግራይን ህዝብ ሊወክል የማይችል የጥፋት ቡድን ነው።

ቡድኑ በአገር ላይ ክህደት በመፈፀም የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ገልጸው የወንጀሉ ተሳታፊ በሆኑ የምክር ቤት አባላት ላይ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱም ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ወጣት ጊዜው የመሸበትን የህወሃት ቡድን በመታገል ለህግ እንዲቀርብ የመከላከያ ሃይሉን እንዲያግዝም ጠይቀዋል።

የህወሃት ጁንታ የራሱን ልጆችና ዘመዶች በተለያዩ የአለም አገራት እያኖረ የድሃውን ህዝብ ልጅ ከትምህርት እያቋረጠ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲወጋ ማሰለፉ በወላጆችም ይሁን በወጣቶቹ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚኒሻ አባላት ጁንታውን “እምቢ” በማለት እጃቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሰጡም አሳስበዋል።

የህወሃት ጁንታ በህግ ማስከበሩ ሂደት በቁጥጥር ስር ውሎ በጦር ፍርድ ቤት ሊዳኝ ይገባዋልም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

(ምንጭ፦ ኢዜአ)

Say Something