አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምእራብ ወለጋ ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥  መንግስት የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ በማገናዘብ የልማት ስራዎችን፣ የሰላም እና የስርዓት ግንባታ ላይ እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ሀይሎች በህዝቡ ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ መሆኑን አስታውቋል።

የጥፋት ሀይሎቹ መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም በጭቃኔ የተሞላ ተግባር በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ነው ብሏል።

የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ከህውሃት ጋር በመሻረክ የኦሮሚያ ክልልን እና ሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ በተለያዩ ወቅቶች የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀት በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመስወድ ችግሮችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብሏል መግለጫው።

ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በተፈፀሙ በእነዚህ ተግባራትም በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንዲፈጠር፣ በስጋት እንዲሞላ እና ከእለት ተእለት እንቅስቃሴ ራሱን ቆጥቡ በረሃብ እና በጥማት እንዲጎዳ እያደረጉ ነውም ብሏል።

በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶችን ጨምሮ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል ብሏል መግለጫው።

ከሁሉም በላይ በጫካ ውስጥ መሽጎ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረው የኦነግ ሸኔ የሽፍታ ቡድን ሰዎችን ጠልፎ በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱ ይታወቃል ያለው መግለጫው፤ በተለያዩ ጊዜያትም የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይም በተመሳሳይ መንገድ ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

የኦነግ ሸኔ ሽፍታ እስካሁን በፈፀማቸው የሽብር ተግባራት በርካታ ቤተሰቦች ተበትነዋል፣ ህፃናትን ያለ አባትና እናት አስቀርቷል ያለው መግለጫው ፥ የህዝቡና የግለሰቦች ሀብትም እንዲጠፋ ማድረጉን አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ያለውን ተልእኮ እና ሀላፊነት ለመወጣት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በስፋት እያከናወነ መሆኑንም 

አስታውቋል።

የህወሓት ተላላኪ የሆነው ይህ የኦነግ ሸኔ ቡድን ህዝቡ እና መንግስት በጋራ በመሆን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው አረምጃ ለመጥፋት መቃረቡንም መግለጫው አመላክቷል።

እየተወሰደ ባለው እርምጃ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ይህ የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ቡድን ተስፋ በመቁረጡ በአንድ ስፍራ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል።

በትናትንው እለትም በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ጨለማን ተገን በማድረግ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉንም የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከሀዝቡ እንዲሁም የፀጥታ እና አስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እነዚህ ሽፍታዎች የገበቡት ቦታ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።

በተፈፀመው ጥቃት ለተሰዉ ወገኖች የተሰማውን ሀዘን የገለፀው የክልሉ መንግስት ለቤተሰቦቻቸው እና ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።

By Eyasu Esayas

Entrepreneur, Writer, Business advocate and Teacher. Nice to have every soul on board. Eyasu do adore the HUMAN Nature. Join the Wonderful Team.

How is that?

Discover more from Essu Center

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading