ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰጡት መግለጫ ዋና ዋና ነጥቦች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰጡት መግለጫ ዋና ዋና ነጥቦች
• ውድ የሀገሬ ህዝብ ሆይ ዛሬ ከሃዲ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ወግተዋል።
• ኢትዮጵያ ባጎረሰ እጇ ባጠባ ጡቷ ተነክሳለች ።
• ላለፉት 20 ዓመታት የቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆን ሀገሬን ወገኔን ህዝቤን ብሎ በብዙ ሺዎች መስዋዕትነት ከፍሎ ቆስሎ ደምቶ ሀገሩንና ህዝቡን የታደገው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ዛሬ ምሽት ከመቐለ ጀምሮ በበርካታ ስፍራዎች በከሃዲው ኃይሎች እና ባደረጁት ኃይል ጥቃት ተፈፅሞበታል።
• ይህ ጥቃት በሀገራችን እስካሁን ከደረሱት ጥቃቶች እጅግ አሳፋሪ የሚያደርገው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰላም ለማስከበር በተለያዩ ሀገራት በተሰማራበት ሀገር በውጭ ኃይል እንኳን አጋጥሞት በማያውቀው ሁኔታ በገዛ ወገኑ ከጀርባው ጥቃት ተፈፀሞበታል።
• በዳንሻ በኩል በአማራ ክልል ላይ የፈፀሙት ጥቃት በአማራ ክልል በነበረው ኃይል ተመክቷል
• የትግራይ ሕዝብ ወገናችን ነው ለጥቂት እኩዮች ሲባል ምንም እንኳን የእኩዮች መሸሸጊያ ዋሻ ቢሆንም ሕዝባችን ላይ ጥቃት አንሰነዝርም ብሎ በትዕግስት በቆየው ሰራዊት ላይ ጥቃት ተፈፅሞበታል
• በመላ ሀገራችን ቀድመው ባሰለጠኑት፣ ባሰማሩትና ባዘጋጁት ኃይል በተለያየ ቦታ እና በተለያየ ከተማ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ ስለሚችሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሊሻው፣ ከፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም በአካባቢያቸው ከሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር ቀያችሁን ሰፈራችሁን እንድትጠብቁ አሳስባለሁ
• የመከላከያ ሰራዊት ከጠቅላይ ሰፈር በሚሰጥ ትዕዛዝ መለዮውን፣ ሀገሩንና ህዝቡን እንዲከላከል ለሚከፍለው መስዋዕትነት ዛሬም እንደተለመደው በታሪኩ ውስጥ የሚታሰብ መሆኑን እገልፃለሁ።
• ይህ እኩይ ኃይል መጥፊያው በመድረሱ በሰላም፣ በንግግር በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮችን ባለፉት ጥቂት ቀናት ካለምንም ሀፍረት በሚዲያ በመውጣት ከየትኛውም የውጭ ኃይል ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን እወጋለሁ ብሎ ሲያውጅ የነበረው ኃይል ይህን ለማመን የሚያስቸግር ንግግር በተግባር ማዋሉን በዚህ ምሽት አረጋግጧል።
• የትግራይ ህዝብ ወገኔ ዘመዴ ሕዝቤ ብሎ ላለፉት 20 ዓመታት በቀበሮ ምሽግ ውስጥ በመሆኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር መስዋዕትነት የከፈለውን አንተን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ያደረገውን የመከላከያ ሰራዊት የደረሰበት ጥቃት ጥቃትህ መሆኑን በመገንዘብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ሀገርህን ከእነዚህ ከሃዲ ኃይሎች እንድትከላከልና በንቃት እንድትጠብቅ አሳስባለሁ።
• ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሳዛኝ አሳፋሪም ተግባር ቢሆንም ዛሬም እንደተለመደው በተደመረ በተባበረ ክንድ ይህንን ከሃዲ ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈርና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልፃለሁ።
ይህ አሳፋሪ ተግባር በማይደገምበት ሁኔታ የሚቀለበስበትን ተግባር መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመተባበር የሚፈፅሙት ይሆናል።
• ለመላው የሀገራችን ህዝቦች አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜው በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጥ መሆኑን እገልፃለሁ።