ጁንታው በአላማጣ በእስረኛ መልክ የያዛቸውን ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃን ወጣቶች አግቶ ወደ ኋላ አፈግፍጓል

አዲስ አበባ፣  ሕዳር 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህወሓት ጁንታ በአላማጣ በእስረኛ መልክ የያዛቸውን ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃን ወጣቶችን አግቶ ወደ ኋላ ማፈግፈጉ ተገለጸ።

የህወሓት ጁንታ በትግራይ ክልል ያሉ ወጣቶችንና ህጻናትን ዩኒፎርም አሰርቶ እያለበሰ ወደ ግጭት እንዲገቡ እያደረገ መሆኑ እንደተደረሰበትም ተገልጿል።

አጥፊው ኃይል መሸነፉን ሲረዳ በእስር ላይ የነበሩ 10 ሺህ  ያህል ሰዎች ከራያ አላማጣ ከተማ ይዞ ሸሽቷል ነው የተባለው፡፡ 

የከተማዋ ነዋሪዎች ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች በአጥፊው ኃይል ለጦርነት እንዳይመለመሉ በመፍራት አካባቢውን ለቀው መሰደዳቸውን ተናግረዋል፡፡  

መከላከያ ሠራዊት አላማጣን በቁጥጥር ስር ማዋሉ፣ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራው በሰላማዊ  ዜጎች ላይ ተጽዕኖ እንዳያስከትል አስፈላጊው ጥንቃቄ  ታክሎበት፣  በውጤታማ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ያሳያልም ተብሏል።

በመከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ የሰው ሃብት ልማትና ሚዲያ አስተባባሪ ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ እንዳሉት ህወሓት በንጹሃን ላይ የሚፈጽመው ግፍ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በአላማጣ አካባቢ የመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ዝግጅት እንዳወቀም በእስረኛ መልክ የያዛቸውን ከ10 ሺህ በላይ ንጹሃን ወጣቶችን ይዞ ወደ ኋላ አፈግፍጓል ብለዋል።

የህወሓት ቡድን በማይካድራና ሌሎች አካባቢ ዘግኛኝ ጭፍጨፋ የፈፀመ የአረመኔዎች ስብስብ በመሆኑ ምን ሊያደርግ እንደሚችል መተንበይ አይቻልም ሲሉም አክለዋል።

Say Something