የሰሜን ዕዝ ከማዕከል  ጋር  የሚኖረው የመገናኛ ሥርዓት  እንዲቋረጥ በማድረግ በጁንታው የህዋሃት የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች ከነ ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ሥር ዋሉ። 

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ለዋልታ በላከው  መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በመንግስት፣ በህዝብና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የተጣለባቸውን አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የጁንታው ህወሓት ሴራ አካል በመሆን የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ጀነራል መኮንኖች፣ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከጁንታው ህወሓት  ጋር በመጣመር ጥቅምት 24, 2013 ዓ.ም  ምሽት  ላይ  በትግራይ  ክልል  የሚገኘው የሰሜን ዕዝ  ከማዕከል  ጋር  የሚኖረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥና የዕዙ የመገናኛ ሥርዓት ለጁንታው የህዋሓት ወንበዴው ቡድን እንዲመቻች  በማድረግ  የተጠረጠረው  ሜጀር ጀነራል  ገብረመድህን ፈቃዱ  ወይም በቅጽል  ስሙ  ወዲ ነጮ   የተባለው ተጠርጣሪ በአገር ክህደት ወንጀል ከነ ግብረ አበሮቹ  በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን  በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ  ተደርጓል።

የአገር  ክህደትን በመፈጸም  በዋናኝነት  የተጠረጠረው ሜጀር  ጀነራል  ገብረመድህን ፍቃዱ ከለውጡ  በፊት በአገር መከላከያ ሠራዊት የአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ሲሆን፥ በሰራዊት ውስጥም  በተለያዩ የሥራ እርከኖች ያገለገለ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ለውጡን ተከትሎም በአገር መከላከያ ሰራዊት የመገናኛ መምሪያ ሃላፊ በመሆን ሲሰራ እንደነበር አስታውሷል፡፡ 

ይሁንና ከመንግስት፣ከህዝብና ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተጣለበትን ከባድ አደራና ሃላፊነት አገር ለማፍረስና ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሰው የጁንታው የህዋሃት የሴራው አካል በመሆን የሰሜን እዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥና በከሃዲዎች ጥቃት እንዲፈፀመበት ከማድረጉም በላይ፤ በውስጣቸው ቦንቦችና የሚሳል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖች የግንኙነት መሳሪዎች ናቸው በሚል ሽፋን ወደ ትግራይ  የጁንታው  ቡድን  ለመላክ  ሲዘጋጅ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በላከው መግለጫ አመልክቷል ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት ጠንካራ ክትትልና ባካሄዱት ኦፕሬሽን  ተጠርጣሪው ሜጀር ጀነራል ገብረ መድህን ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶቻቸው በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

በቀጣይም ከጁንታው የህዋሃት የጥፋት ቡድን አገር የማተራመስና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በአገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትንና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በህግ ተጠያቂ  እንዲሆኑ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

By Eyasu Esayas

Entrepreneur, Writer, Business advocate and Teacher. Nice to have every soul on board. Eyasu do adore the HUMAN Nature. Join the Wonderful Team.

Say Something