በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ መግለጫ
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይና ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦሬል ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ትናንት በብራስልስ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ፈታኝ ጊዜ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም የሰብዓዊ መብትና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች ጥሰት በጣም እንዳሳሰባቸው ለአቶ ደመቀ መግለፃቸውን ጠቅሰዋል።ይህም ቀጠናውን ቀውስ ውስት እየከተተ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያና በቀጠናው በተለይም በሱዳን በሚታየው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ላይም ሁለቱ ባለስልጣናት መወያየታቸውንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ህግ ሊከበር እንደሚገባ በውይይቱ ማመለከታቸውን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ለሰላማዊ ዜጎች ፣ ለተጋላጭ ለሆኑ ቡድኖችና እንዲሁም ለተፈናቃዮች ሰላማዊና ነፃ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲሁም ጥበቃ እንዲደረግ በአውሮፓ ህብረት ስም ጥሪ አቅርቤአለሁ ብለዋል።
ጆሴፍ ቦረል አያይዘውም«የአውሮፓ ህብረት መልእክት ግልፅ ነው።ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹና እርዳታን ተደራሽ እንዲያደርጉ ለሁሉም ወገኖች ጥሪ እናቀርባለን። ግጭትን ማቆም የትኛውም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት ማስወገድ፣ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከተሾሙ የከፍተኛ ልዑካን ጋር በመተባበር ለውይይት በር መክፈት ይገባል።ይህም ተጨማሪ አለመረጋጋትን ለማስቀረት ብቸኛው መንገድ ነው ፡፡» ብለዋል።