በትግራይ ክልል የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ አብዛኛው በቁጥጥር ስር ውሏል- ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው
የፌዴራል ፖሊስ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት በወቅታዊ የሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው እንዳሉት በትግራይ ክልል ጽንፈኛው የህወሓት ታጣቂ ቡድን የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እና ሚልሻዎች በቅንጅት በወሰዱት እርምጃ አብዛኛው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የተቀረውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ መንግስት እና ህዝቡ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞሩ ለማስቻል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቀሪው ጊዜያትም ሁሉም የጸጥታ እና ደህንነት መዋቅሩ በአንድነት ተደራጅተው በመስራት በዚህ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራውን ኃይል ከስረመሰረቱ መንቀል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመንግስትና የህዝብ ተቋማትን መጠበቅ የህዝቡ የዕለት ዕለት ኑሮ እንዳይስተጓጎል ማድረግ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ እንዲሆን ይሰራልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ህብረተሰቡ በየአካባቢው በመደራጀት ፀጉረ ልውጦችን ለጸጥታ ኃይሉ በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግና መንግስት ለሚያደርገው ጥሪ ዝግጁ እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፣ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እና ኃላፊነት ከማይሰማቸው የመገናኛ ብዙኃን እየተላለፉ ያሉ የሀሰት መረጃዎችን ከማሰራጨትና ከመቀበል መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ ከትክክለኛ እና ከሚመለከታቸው አካላት መረጃውን በማጣራት እና በመቀበል ከሰራዊቱና ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ወቅታዊ መረጃዎች ለህብረተሰቡ የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
(በአስታርቃቸው ወልዴ)